ምስጢረ ንስሐ

ምስጢረ ንስሐ

ምሥጢረ ንስሐ

ንስሐ ፦ ነስሐ ተፀፀተ ካለው የተገኘ ሲሆን ፤ ንስሐ ማለት በሠሩት ኃጢአት መፀፀት ፣ ማዘን ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መወሰን ማለት ነው። ንስሐ ከዘለዓለማዊ ፍርድ የሚያድን ፤ ዘማዊውን እንደ ድንግል ፤ ሌባውን መጽዋች የሚያደርግ በፊት ከተሠራው ኃጢአት ንጹህ አድርጎ ፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርግ ምሥጢር ነው ።

ከንስሐ በፊት

  • መፀፀት
    አንድ ክርስቲያን በድፍረትም ይሁን በስህተት “የሠራው በደል” መጻሕፍት በማንበብ ፣ ከመምህራን ተምሮ ፣ የስብከት ካሴት አዳምጦ ፤ ህሊናው ወቅሶት ፣ ወይም በሌላ በአንድ ምክንያት ስህተት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ተፀፅቶ ከእግዚ አብሔር ለመታረቅ (በደሉን ለማስተስረይ) የሚያደርገው ጉዞ ንስሐ ይባላል ። በሠራው በደል ሳይፀፀት ፤ ለጊዜው ህሊናውን ስለረበሸው ብቻ ንስሐ የሚገባ ሰው ፤ ከስሐውን በኋላ ወደ ቀደመ ሕይወቱ ሊመለስ ይችላል ። ምክንያቱም ፡ ንስሐ የገባው ፡ በሠራው በደል ከልቡ ተፀፅቶ ሳይሆን ፤ በስሜት ተነሳስቶ ነውና ፤
  • ኃጢአትን መጥላት
    በበደላችን ከተፀፅትን በኋላ የሰራነውን በደል መጥላትና ወደፊትም መሥራት እንደሌለብን ራሳችንን ማሳመንና ከኃጢዓት መንገድ መራቅ ማለት ነው ።
  • ከንስሐ በኋላ ስላለው ሕይወት መወሰን
    አንድ ምዕመን ንስሐ ከመግባቱ በፊት ለወደፊቱ የሚኖረውን ሕይወት አስቀ ድሞ መመርመርና መወሰን ይገባዋል የእግዚአብሔን ቃል ስንሰማ ለጊዜው ልባችን ሊነካ ፣ ምን እናድርግ ልንል እንችላለን ። የሐ ሥ 2 ፥ 37 ። ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዓለሙን ወደመምሰል እንደማንመለስ አስቀድመን ራሳችንን መመርመር አለብን ። ብዙዎቹ በስሜት ወደ ክርስትና ከገቡ በኋላ ፤ በጊዜያዊ ነገር ተታለው በድንገት ከሃይማኖት መንገድ ወጥተዋልና ።

በንስሐ ጊዜ

አንድ ምዕመን ካለፈ በደሉ በንስሐ ታጥቦ በአዲስ ሕይወት ራሱን ለማስተካከልና ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ከወሰነ በኋላ የንስሐ አባት ሊኖረው ይገባል ። ጌታችን “ካህናትን” ራሱን ወክለው መንጋውን እንዲጠብቁ “በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” (ማቴ 8 ፥ ዮሐ 21 ፥ 15 ። ማቴ 16 ፥ 19) በማለት መንጋውን እንዲጠብቁ ሾሟቸዋልና። አንድ ክርስቲያን በሕይወት ሲኖር ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚመራው ፤ ሲሳሳት ንስሐውን ተቀ ብሎ ቀኖና በመስጠት ከእግዚአብሔር የሚያስታርቀው የንስሐ አባት የግድ ሊኖረው ይገባል።

ንስሐ የሚገባው ምዕመን በካህኑ ፊት በሚቀርብበት ጊዜ የሚከተሉትን ማሟላት አለበት

  • የሠራውን ስህተት በሙሉ ማስታወስ
    ቀኖናው የሚሰጠው እንደ በደሉ ዓይነት ስለሆነ የሠራውን ማስታወስ አለበት ፤ በቃሉ የሚረሳው ከሆነም በጽሁፍ መመዝገብ ያስልጋል ።
  • ይቀንሱ (ሳይከፍሉ) በሙሉ መናገር
    “ይህን ብናገር ሰው ምን ይለኛል ?” ብሎ ከባዱን (የሚያሳፍረውን) ነገር መደበቅ የለበትም። ሲሰራው ያላሳፈረውን ሲናገረው ሊያፍርበት አይገባም። አንድ ጊዜ ተናግሮ ከህሊናው ካላስወጣው ሁሌም ሲረብ ሸው ይኖራልና።“እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ ሸክማችሁን አራግፋለሁ” ማቴ 11 ፥ 28ተብሏልና በትክክል አስታውሶ መናዘዝና የኃጢአትን ሸክም ማራገፍ ይገባል። ስለ በደላችን በምንናዘዝበት ጊዜ ግን ፤ ከዕገሌ ጋር ፤ በዚህ ጊዜ ፤ በዚህ ቦታ ፤ ይህን አድርጌያለሁ እያልን ፤ ቦታውን ፤ ጊዜውን የሌላ ሰው ስም በዝርዝር እንድንናገር አንገደድም ፣ የሠራነውን በደል ብቻ “ጣዖት አምልኬያለሁ ፤ ሠርቄያለሁ ፤ አመንዝሬያለሁ” በማለት በጥቅሉ መናገር እንችላለን ።
  • ኑዛዜ (ራስን መክሰስ)
    በራሳችን ድካም የሠራነውን በደል “ዕገሌ አሳስቶኝ” እያሉ ሌላውን ሰው ስለ እኛ ስህተት ተጠያቂ ማድረግ ሳይሆን ፣ አንደበታችንን ከሳሽ ህሊናችን ምስክር አድርገን በመጨከን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት መክሰስ ነው ። አምላካችን የልባችንን መመለስ ፣ አይቶ የሰራነውን በደል ሁሉ እንዳልተሠራ አድርጎ ያነጻናል ። በደልን በንስሐ ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ነውና።

አንድ ምዕመን ንስሐ ከገባ በኋላ የሚከተሉትን በቅደም ተከተል ማድረግ አለበት?

  1. የተቀበለውን ቀኖና በትክክል መፈጸም
    ቀኖና የግሪክ ቃል ሲሆን : መለኪያ ማለት ነው ። ካህኑ ለበደለው ምዕመን እንደ ሃይማኖቱ ጽናት ፣ እንደ አእምሮው ስፋት ፤ የሠራውን በደል መጥኖ ቀኖና ከሰጠው በኋላ እንደታዘዘው መፈጸም አለበት ። የነነዌ ሰዎች ፣ ት. ዮና 3 ፥1 ። ንጉሡ ህዝቅያስ ፣ ኢሳ 38 ፥ 1 ። ቅዱስ ጴጥሮስ ሉቃ 22 ፥ 54 ። እና ሌሎችም ይቅርታን ያገኙት ፤ በበደላቸው ተጸጽተው በማልቀሳቸውና ንስሃ በመግባታቸው ነው ። በንስሐ ወቅት ፡መሬት ላይ መተኛት ምግብ መቀነስ ፣ ከዓለማዊ ነገሮችና ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይመቹ ጓደኞች መራቅ ያስፈልጋል ። በንስሐ ጊዜ እንዳናደርግ ከታዘዝነው ነገር ራሳችንን በመግዛት መቆጠብ አለብን ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ወደ ድኅነት ከጠራን በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደተውነው ድካማችን መመለስ የለብንም። የጊዜውን ሳይሆን የመጨረሻውን ማሰብ አለብን ። 2 ጢሞ 4 ፥10 ። መዝ 6 ፥6 ።
  2. በደላችን በንስሐ እንደሚሰረይልን ማመን
    ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው በደላችንን ለመደምሰስ ስለሆነ ከበደላችን ሊያነጻን የታመነ አምላክ ነው ። ከሠራነው ብዙ ኃጢአት አንጻር የሚሰጠን ቀኖና ትንሽ መስሎ ቢታየንም ። ማሰብ ያለብን የራሳችንን በደል ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቸርነት ነው ። ከእኛ በደል የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራው እጅግ ይበልጣልና የታዘዝነውን ፈጽመን የቀረውን እንደቸርነትህ ማለት ይገባል ። “የታዘዛችሁትን ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ” ተብለናልና ። ሉቃ 17 ፥ 10 ።
  3. በሥጋውና በደሙ መታተም (መቁረብ)
    አንድ የተራበ ሰው እጁን ስለታጠበ ብቻ አይጠግብም ። የግድ ምግብ መብላት አለበት ። ንስሐ ማለት መታጠብ ፣ ከእድፍ (ከኃጢአት) መንጻት ማለት ሲሆን ፤ ድኅነት የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው ። ዮሐ 6፥33 ። ብዙዎቹ መቁረብን እንደ ትርፍ ነገርና በዕድሜ የተገደበ (ለሽማግሌ ብቻ) አድርገው ስለሚቆጥሩት ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም ። ነገር ግን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ቅዱስ ቁርባን የግድ ያስፈልገዋል ። ቀኖና የተቀበልንበት በደላችን የሚሰረየው ሥጋውን ስንበላ ፣ ደሙንም ስንጠጣ ነውና ።
  4. ሁሌም ለንስሐ መዘጋጀት
    ንስሐ ከገባንና ከቆርብን በኋላ እንደገና በኃጢአት ልንወድቅ እንችላለን። አምለካችን “ለምን ንስሐ አልገባህም እንጅ ለምን ኃጢአት ሠራህ? አይልምና” ሁለተኛ ስንበድል ሀፍረት ሳይሰማንና ከኃጢአት መላቀቅ ካልቻልሁ በየጊዜው የንስሐ አባቴን ከማስቸግር አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል በማለት ፡ ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድተወው ፡ ክፉ ሀሳብ በአምሯችን ሊፈታተነን ይችላል ።
    ነገር ግን ከንስሐ በኋላ እንደ መላእክት በቅድስና ብቻ እንኖራለን ማለት ሳይሆን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ፤ ሰባት ጊዜ ይነሳል” ምሳ 24፥ 16 ። እንደተባለ ፡ አምላካችን ብንወድቅ ሊያነሳን ፤ ብንጠፋ ሊፈልገን ፤ ብንርቅ ሊያቀርበን ፤ በኃጢአት ብንረክስ ሊቀድሰን (እንደ ባዘቶ ሊያጠራን) የታመነ አምላክ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ ፤ በኃጢአታችን ሳንደበቅ ፤ ዘወትር ለንስሓ መዘጋጀት አለብን። ኢሳ 1 ፥ 18 ።