ምሥጢረ ሥላሴ

ምሥጢረ ሥላሴ

ሠለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት ነው ። በዚህ ትምህርት የአምላክን አንድነት ሶስትነት እንማራለን ።

የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በምንማርበት ጊዜ ከሂሳብ ቀመር ህግ አስተሳሰብ ውጭ ሆነን ነው ። ምክንያቱም መንፈሳዊዉ ሥጋዊዉን ጥበብ (ፍልስፍና) ይመረምረዋል እንጅ መንፈሳዊ ጥበብና ምሥጢር በዓለማዊ ዕውቀት ምርምር ሊደረስበት አይቻልምና ። የሃይማኖት ነገር ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊና በሃይማኖት ሆኖ በመንፈሳዊነት የሚታወቅና የሚታመን ነው ።

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን

“ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ዘፍ 1 ፥ 26 ። ። ከዚህ ቃል በፊት እግዚአብሔርን የሚመስል ፍጡር መኖሩን የሚገልጽ ባለመኖሩ “በመልካችን…” የሚለው አምላክ ከአንድ በላይ የሆነ የራሱ መልክ እንዳለው ያስረዳል። እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ማንም ረዳት እንዳላስፈለገው በኢሳ ፡ 40 ፥ 12 ። ላይ ተጽፎ እናገኛለን ። በመሆኑም “በመልካችን..”የሚለው ሶስትነቱን (ከአንድ በላይ መሆኑን) ፤ “አለ” የሚለው ደግሞ አንድነቱን ይገልጽልናል ።

“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ 3 ፥ 22 ። እግዚአብሔር በአካልና በስምና በግብር ሶስትነት ባይኖረው ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” በማለት ይናገር ነበር ። “ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ግን ብዙ ቁጥርን አመላካች በመሆኑ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።

ዘፍ 11፥7 ። “ኑ እንውረድና ቋንቋቸውን እንደባልቀው አለ” ይህ ቃል አንዱ ሌሎቹን ኑ እንደሚል እንረዳለን ። በዚህም እግዚአብሔር ለአምላክነት ሥራው የማንንም እርዳታ እንደማይፈልግ የሚታወቅ ሲሆን በውስጡ ከሁለት በላይ እንደሆነ አንዱ ሌሎቹን “ኑ” በማለቱ ያስረዳል ።

ዘፍ 18 ፥ 1 ። እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ስር ለአብርሐም ተገለጠለት ። አብርሐምም ዓይኑን አነሳና ሶስት ሰዎችን አየ የሚለው እግዚአብሔር በሶስትነቱ በሰዎች አምሳል ለአብርሐም መገለጡን በቁጥር ሶሰት ብሎ ያስረዳል ። ሀሳቡን ግልጽ ለማድረግ እግዚአብሔር ከሶስት ሰዎች ጋር ወይም ከሁለት መላእክት ጋር ተገለጠለት አይልም ። መላእክትም ሆኑ ሰዎች በዚህ ሥም አይጠሩም ኢሳ 42 ፥ 8 ። እስከዚህ ድረስ ብዛትን ብቻ ሲያመልክት የነበረው በዚህ ላይ ሶስት ብሎ ለይቶ ስለተናገረ እግዚአብሔር ሶስትነት ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ።

የእግዚአብሔር ሶስትነት

እግዚአብሔር ፤ በስም ፤ በግብር ፤ በአካል ፤ ሶስት ነው ።

የስም ሶስትነት

አብ ፡ ወልድ ፡ መንፈስ ቅዱስ፡በመባል ነው ። “ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ማቴ ፳፰ ፥ ፲፱ ። የአብ ፍቅር ፤ የወልድ ፀጋ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ፤ የሚለው ቃል ሶስትነቱን በግልጽ ያስረዳል ። 2ቆሮ 13 ፥ 14 ።

ስሙ (የወልድ) ፤ የአባቱ ስም ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ የተጻፈባቸው ። ራዕ 14 ፥ 1 ። ከላይ የተገለጹት የእግዚአብሔርን የስም ሶስትነት ያስረዳሉ ።

አብ ፤ በራሱ ሥም አብ ይባላል እንጅ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም ። ሶስቱም በየስማቸው ይጠራሉ ። ሃይ አበው ምዕ 11. ክፍል 1 ፡ 7 ።

“ሥላሴ” ማለት ሶስትነት ማለት ሲሆን ፤ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሶስትነት ጥቅል ስም ነው ። “ሥላሴ” በምን ልበት ጊዜ አብ ፤ ወልድ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፤ ማለታችን ነው ።

የግብር ሶስትነት

ግብር ሥራ ማለት ሲሆን ፤ በዚህትምህርት የእግዚአብሔርን የግብር ሶስትነት አብ አባት ፤ ወልድ ልጅ ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ መሆናቸውን እናያለን ።

አብ ማለት አባት (ወልድን የወለደ) ። ማቴ 3፥17 ። አስራጺ ፡ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ። ዮሐ 15፥26 ።

ወልድ ፤ ተወላዲ (ከአብ የተወለደ) ። ሉቃ 1 ፥ 35 ። መንፈስ ቅዱስ ማለት ፤ ሰራጺ (ከአብ የሰረጸ) ። ዮሐ ፲፭ ፥ 26 ። ማለት ነው ።

አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ (ሕይወት) ፣ በማለቱ ። የግብር ሶስነቱ የስሙን ሶስትነት ይገልጻል ። ይህ ማለት ግን አብ አባትና አስገኝ ፣ ስለተባለ ከአብና ከወልድ አይቀድምም አይበልጥም ፤ ወልድም ከአብ አያንስም ፤ ከመ ንፈስ ቅዱስ አያንስም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ አያንስም ። ሁሉም እኩል በአንድነትና በሶስትነት ይመሰገናሉ ።

የአካል ሶስትነት

ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈሰ ቅዱስ ለየራሳቸው ፍፁም ገጽ ፣ ፍፁም መልክ ፣ ፍፁም አካል፣ አላቸው ።

ገጽፊት ማለት ሲሆን፣ ከአንገታችን በላይ የሚታዩት የሰውነት ክፍሎቻችንን ዓይን ፣ ጆሮ…. የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ።

መልክበእያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች (እግር ፣ እጅ ፣ ራስ ፣ ፀጉር ፣ ዓይን ፣ ጆሮ…..) ተብለው ሲቆጠሩ ነው ።

አካል በአጠቃላይ ሙሉው የሰውነታችን ክፍል ነው ። የፍጡራን አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚመጠን ፤ የሚወሰን ፣ ሲሆን የሥላሴ አካል ግን ፤ የማይታይ ፣ በእጅ የማይዳሰስ ፣ በቦታ የማይወሰን ፣ በሁሉም ሙሉ ነው ። መዝ 138 ፥ 7 ።

የእግዚአብሔር የአካል ሶስትነት ። በማቴ 3 ፥16 ። እንደተገለጠው አብ በደመና ፣ ወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመሆን በግልጽ ታይቷል ። በሌላም በኩል ለአብርሐም በሶስት ሰዎች አምሳል የተገለጠለት ፣ በአካል ሶስት መሆኑን ሲያስረዳው ነው ። የሥላሴ ሶስትነት ከሰዎች የሂሳብ ቀመር ልዩ ስለሆነ (ቅድስት ሥላሴ) ልዩ ሶስትነት ይባላል ። በሂሳብ ህግ አንድ ሲሆን ሶስት…. የሚሆን ነገር የለምና ። የየራሳቸው የሶስትነት ፣ ሥም ፣ ግብር ፣ አካል ፣ አላቸው ።

የእግዚአብሔር አንድነት

የእግዚአብሔር ሶስትነት በሶስት ነገሮች በስም ፣በግብር፣በአካል፣ ብቻ ሲሆን በሌላው ሁሉ ለምሳሌ በባህርይ በህልውና ዮሐ 14 ፥ 8 ። በፈቃድ ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር… ፣ አንድ ነው ። ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በተለያየሥራና ደረጃ ተጽፎ ብናገኝም የስማቸውን የግብራቸውንና የአካላቸውን ሶስትነት ለመግለጽ እንጅ በአንዱ ሥራ ሁሉም አሉበት ። ዓለምን ፈጥሮ እየገዛ ያለ ፣ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነ ፣ አምላክ አንድ ብቻ ነው ። ኤፌ 4 ፥ 5 ።

ኩነት (ከዊን)

ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት) አሏት ፤ እነሱም ፤ ልብ (ማሰብ) ፤ ቃል (መናገር) ፤ እስትንፋስ (ሕይወት) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ።

የእግዚአብሔር ሶስትነት በሰው ነፍስ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል ። ይኸውም አብ በልብ (ማሰብ) ፣ ወልድ በቃል (መናገር) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ። በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል ፣ ሕይወት አለ ። ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም ሶስት ስም፤ ሶስት ግብር ፤ ሶስት አካል ፤ ቢኖረውም አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥፬ ። ሚል 2 ፥ 10 ።

የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች

ፀሀይ

አካል (መጠን) ብርሃን ሙቀት አላት ። በአካሏ አብ ፣ በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።

ውሃ

ይዘት(ስፋት) ፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ። በይዘቱ (በስፋቱ) አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ። ሌሎቹም በምሳሌነት የሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ። ነገር ግን በምሳሌነታቸው ለማስተማር እንጅ የአምላክን ባህርይ የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።